ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስርና አንድነት በማጎልበት ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስርና አንድነት በማጎልበት ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለፁ።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ”በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ እና የአረጋውያን እንክብካቤ መርሃ ግብር አከናውነዋል፤ የቁሳቁስ ስጦታም አካሂደዋል።

ወጣቶቹ የአዳማ ዶሮ እርባታ ክላስተር እና የስማርት ሲቲ ኢንሽቲቮችን ጎብኝተዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የህዝቡን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከርና አብሮነትን ለማጎልበት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። መርሃ ግብሩ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲጠናከር ከማስቻል ባለፈ በልማት ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። በተያዘው ክረምትም በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰፊ ዕውቀትና ጉልበት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ከድር እንዳልካቸው በበኩላቸው ወጣቶች ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን ጉልበትና ዕውቀታቸውን መጠቀም አለባቸው ብለዋል። የክልሉ ወጣቶች ዘርፈ ብዙ የልማትና ሪፎርም ስራ ውስጥ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ተሳታፊ ወጣቶችም ልምድና ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ጠይቀዋል። በክልሉ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ፣ በእናቶችና አረጋውያን ቤት እድሳትና ግንባታ፣ በደም ልገሳና ሌሎች በጎ ፍቃድ አገልግሎት በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዳማ ከተማ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሸናፊ አጀማ፣ በከተማው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በስፋት እየተከነወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተለይም በአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት፣ በደም ልገሳ፣ በማጠናከሪያ ትምህርትና በሌሎች ዘርፎች የበጎ ፈቃድ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል። ከተማ አስተዳደሩ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የስማርት አዳማ ፕሮግራም ቀርፆ እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ከወረቀት ንክኪ ለማድረግ ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራ እተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

Please follow and like us: