“በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በትኩረት እንሰራለን” ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር)

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተቋቋመውን ጥምረት ወክለው በተባበሩት መንግስታት ዋና መስሪያ ቤት በተዘጋጀው የእውቅና ሽልማት መርሃ ግብር ላይ ነው። በኒውዮርክ በተዘጋጀው በዚህ መርሃግብር ኢትዮጵያ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ለመከላከል በሰራችው ስራ በተባበሩት መንግስታት ስነ ህዝብ ሽልማት ላይ እውቅና አግኝታለች፡፡

ሚኒስትሯ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የወሰዳችውን የህግ፣ የፖሊሲና የፕሮግራም እርምጃዎች አብራርተዋል። ይህ አለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት መንግስት ለስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ለማብቃት ያለውን ቁርጠኝነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆንም ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ትኩረት ሰጥተን በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ስነ ህዝብ ሽልማት እ.ኤ.አ በ1981 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የተመሰረተ ሲሆን በየአመቱ በስነ ህዝብና ስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ልዪ አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ይሰጣል፡፡ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተቋቋመው ጥምረት እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ተመስርቷል።

 

Please follow and like us: