የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶች ሰብዕናን በመቅረጽ ዝቅ ብለው ሀገራቸውንና ወገናቸውን እንዲያገለግሉ እና ጠንካራ የስራ ባህልን እንዲያዳብሩ አስችሏል – ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶች ሰብዕናን በመቅረጽ ዝቅ ብለው ሀገራቸውንና ወገናቸውን እንዲያገለግሉ እና ጠንካራ የስራ ባህልን እንዲያዳብሩ አስችሏል ሲሉ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ገለጹ።

በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በመዟዟር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወኑ ያሉ የወጣት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኞች ቡድን በሐረሪ ክልል በመገኘት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አከናውነዋል። በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንደተናገሩት በጎ ፈቃደኞቹ በየክልሉ በጎ ተግባራት በማከናወን ላይ ናቸው። ከእነዚህ ተግባራት ጎን ለጎንም የየክልሉን ባህል፣ ወግ እና እሴቶችን እንዲያውቁ ከማድረጉ በተጨማሪ ወጣቶች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲዳብር እድል መፍጠሩን ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶች ሰብዕናን በመቅረጽ ዝቅ ብለው ሀገራቸውንና ወገናቸውን እንዲያገለግሉ፣ የስራ ባህልን እንዲያዳብሩ ከማስቻሉ ባለፈ የሀገሪቱን ህዝብ አብሮነትና አንድነት አጠናክሯል ሲሉም ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ረምዚያ አብዱልዋሃብ በክልሉ 46ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉበት የሚገኝ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። ወጣቶቹ የሚያከናውኑት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች 103ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መተሳሰብ እና መረዳዳትን ያጎለበትንበትና የህሊና እርካታ ያገኘንበት ነው ሲሉ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተናገሩ።

በሀገር አቀፍና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች በሚሳተፉበት ወሰን የለሽ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ላይ ከተሣተፉ ወጣቶች መካከል ወጣት ድግሪ ሃይለማርያም ይገኝበታል። ወጣቱ እንዳለው በጎ ፈቃደኝነት በቋንቋና ብሔር የሚገደብ ሳይሆን በራስ ተነሳሽነት የሚሰራና የሂሊና እርካታ የሚያስገኝ ተግባር ነው። ሁሉም ወጣቶች የህሊና እርካታ በሚሰጠው የበጎ ፈቃድ ተግባር ስራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ማበርከት ይጠበቅበታል ሲልም ተናግሯል። በጎነት ለራስ ስንቅ ነው፤ በዚህ በጎ ተግባር ላይ በመሣተፌ ደስታ ተሰምቶኛል ያለችው ደግሞ ወጣት ሁሉአገርሽ ሙሉቀን ናት። በክረምትም ሆነ በበጋ አቅመ ደካሞችንና ህጻናትን መደገፍ፣ በሀገር ልማት ላይ አስተዋጽዎ ማበርከት ከአንድ ወጣት የሚጠበቅ ተግባር ነው ብላለች። ይህን ተግባር ወጣቱ ማጠናከር ይጠበቅበታል የሚል መልዕክትም አክላለች። በጎ ፈቃደኝነት ማለት ካለህ ነገር ላይ ቀንሰህ ለአቅመ ደካሞች እና ትናንት ለእኛ ለደከሙ አባትና እናቶች መድረስ እና ማካፈል ነው ያለችው ወጣት ሐናን አህመድ፤ በዚህ ተግባር መሳተፌ የህሊናና የመንፈስ እርካታ አግኝቼበታለሁ ብላለች።

ወሰን ተሻግረን ሀገርንና ዜጎችን እየጠቀምን እንገኛለው ያለችው ወጣት ሀናን፤ ሌሎች ወጣቶችም በክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፋለች። በየአረጋውያን ቤት እድሳት፣ በችግኝ ተከላ፣ በህጻናት ክብካቤ እና በጎዳና ጽዳት መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት ወጣቶቹ በሐረሪ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን ቀጣይ ጉዟቸው ወደ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደሆነም ተገልጿል።

Please follow and like us: