የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የአልባሳት ድጋፍ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ተቋማት አደረገ

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ (UAE) ጋር በመተባበር የተለያዩ በክረምት ወቅት መጠቀሚያነት የሚውሉ አልባሳት ለየወደቁትን አንሱ የነዳያን ማህበር እና ለሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት አደረገ።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ እንደተናገሩት፤ ድጋፋ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስተባባሪነት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ነው። ድጋፉ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያንና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በማስጠለል የበጎ አድራጎት ስራ እየሰሩ እና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውንም እየተወጡ የሚገኙ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ገልጸዋል። የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ለተቸገሩ ወገኖች እያደረጉት ያለውን የድጋፍና እንክብካቤ ተግባር ስራ አስፈፃሚዋ አድንቀዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ እና ተቋማቱ ላበረከቱት አስተዋጽዖም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተጠቃሚ ወገኖች ስም አመስግነው ድጋፉ የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝም በዚሁ ወቅት ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደፊትም የተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላትን በማስተባበርና ሀብት በማሰባሰብ በመልካም ስራቸው የወገን አለኝታ የሆኑ መሰል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል ብለዋል። የግል ባለሃብቱ፣ ህብረተሰቡና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከሰብዓዊነት በመነጨ ለበጎ ስራ የሚተጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን አቅም በፈቀደ ሁሉ እንዲደግፉ፣ ጥረታቸውን እንዲያበረታቱና የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ የዜጎች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሮ ዋፋ አህመድ በበኩላቸው ኤምባሲው ከሚኒስቴሩ ጋር በጋራ በመሆን እገዛ ለሚሹ ወገኖች እና ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። ወደፊትም መሰል ድጋፎችን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በዕለቱ የስራ ኃላፊዎቹ በድጋፍ መልክ ለመስጠት የተዘጋጁትን አልባሳትና እና ብርድ ልብስ ለተቋማቱ ተወካዮች አስረክበዋል።

የየተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ኤምባሲውን አመስግነዋል። ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

 

Please follow and like us: