ወሰን ተሻጋሪ ወጣት በጎ ፈቃደኞች የክልሉን ወጣቶች ለበጎ ፈቃድ ስራ እንዲነሳሱ አድርገዋል

ወሰን ተሻጋሪ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ያከናወኗቸው በጎ ተግባራት ሌሎች የክልሉ ወጣቶች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲነሳሱ ማድረጉን የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።

ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በአፋር ክልል ዱብቲ ሆስፒታል የበጎ አድራጎት ተግባራትን አከናውነዋል። በዕለቱ የተገኙት የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡመር ኑሩ እንዳሉት ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች ያደረጉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ለሌሎች ወጣቶች አርአያ ሆኗቸዋል። ህሙማንን መጠየቅና መርዳት፣ የደም ልገሳና የአካባቢ ንፅህና ተግባራት ማከናወናቸውን የገለፁት አቶ ኡመር፤ ይህም የአካባቢው ወጣቶች ለበጎ አድራጎት ስራ እንዲነሳሱ ማድረጉን ተናግረዋል።

የዱብቲ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ሁሴን አደን(ዶ/ር) በበኩላቸው በሆስፒታሉ የሚገኙ ታካሚዎችን ለማገዝ በደም ልገሳና በአካባቢ ፅዳት የተከናወኑት ተግባራት የህይወት አድን አካል ናቸው ብለዋል። ታካሚዎችን መጠየቅ መቻላቸው ደግሞ የአዕምሮ መነቃቃትና የስነ ልቦና ፈውስ የፈጠረላቸው ነው ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራቱ ላይ የተገኙት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እንደገና በፍቃዱ ደግሞ በጎነትና የደግነት ስራ በወሰን ያልተገደበ መሆኑን ገልጸዋል። የወሰን ተሻጋሪ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሶሰተኛ ጊዜ የተከናወነ መሆኑን አስታውሰው ከዓመት ወደ ዓመት የተሳታፊ ወጣቶች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል።

Please follow and like us: