ሴክተሩ ሰፊ ተልዕኮና ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ሚናወን በአግባቡ እንዲወጣ ተናቦና ተደጋግፎ መስራት ይገባል – ክብርት ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

ሴክተሩ ሰፊ ተልዕኮና ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ሚናወን እንዲወጣ ተናቦና ተደጋግፎ መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

የሴቶችና ማህበራዊ ሴክተር የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ስትራቴጂክ ጉዳዮችና ዋና ዋና ግቦች ላይ የፌዴራልና የክልል የቢሮ ኃላፊዎች ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እንደሀገር የገጠሙትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ በቅንጅት ርብርብ በመደረጉ አበረታች ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል። ለዚህም በየደረጃ የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ድርሻ የላቀ መሆኑን ክብርት ሚኒስትሯ አንስተዋል፤ ለተደረገው ጥረትና ርብርብና እውቅና ሰጥተዋል።

ሆኖም እንደሴክተር ወጥ እቅድ በማዘጋጀት፣ በመረጃ አያያዝና ልውውጥ፣ በመዋቅርና አደረጃጀት፣ በበጀትና ቁሳቁስ፣ በእውቀትና ክህሎት፣ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ረገድ አሁንም ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል። ከ10 እና ከ5 አመቱ የመካከለኛ ዘመን እቅድ የተቀዳና ያለፈው ዓመት አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ የ2017 እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸው፥ በሴክተሩ ተደራሽ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።

ሴክተሩ ሰፊ ተልዕኮና ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ይህን ሚናወን በሚገባ መወጣት እንዲቻል ተናቦና ተደጋግፎ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ የአድቮኬሲና የስልጠና መድረኮችን፣ የትብብርና ቅንጅትን ስራዎችን፣ የድጋፍና ክትትል ተግባራትን፣ የግምገማና የግብረ መልስ ስርዓትን የማጠናከር ይሰራል ብለዋል። ከፕላን ልማት ሚኒስቴር እና ከክልሎች ጋር በመነጋገር በመዋቅር ደረጃ ያለውን ችግር ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

 

Please follow and like us: