የስጋ ደዌ በሽታ ስርጭትና ተጽዕኖ ማስወገድ ላይ ያተኮረ አህጉር አቀፍ ጉባኤ በቀጣዩ አመት በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

የስጋ ደዌ በሽታ ስርጭትና ተጽዕኖ ማስወገድ ላይ ያተኮረ አህጉር አቀፍ ጉባኤ በቀጣዩ አመት በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ተካሄዷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሚስተር ሺባታ ሂሮነሪ፣ የአለም ጤና ድርጅት የስጋ ደዌ ማስወገድ በጎ ፈቃድ አምባሳደር እና የኒፖን ፋውንዴሽን ሊቀመንበር ሚስተር ዮሂ ሳሳካዋና ልዑካቸውን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚሁ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጉባኤው ስጋ ደዌ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአፍሪካውያን ሀገራት ትብብርና ቅንጅትን ለማጠናከር የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ጉባኤው በአፍሪካ የስጋ ደዌ በሽታ ስርጭትን ለመግታት፣ መገለልና ፍረጃ ለማስቀረት ብሎም ተገቢውን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የድርጊት መርሀ ግብር ለመንደፍም ያግዛል ብለዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጉባኤውን ከስጋ ደዌ ብሔራዊ ማህበርና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተሳካ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ እንደሚጀመር አስታውቀዋል። ሚስተር ዮሂ ሳሳካዋ በበኩላቸው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ጉባኤውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም ጤና ድርጅት፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከሳሳካዋ የስጋ ደዌ ኢኒሼቲቭ እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል። ጉባኤው በቀጣዩ አመት የካቲት ወር ላይ ለማካሄድ እቅድ መያዙን እና በጉባዔው ከተለያዩ የአለምና የአፍሪካ አገራት እና በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት የተወጣጡ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

 

Please follow and like us: