የብሪክስ የወጣቶች ጉባኤ በአባል አገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር ይከፍታል – ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና

የብሪክስ የወጣቶች ጉባኤ በአባል አገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር ይከፍታል ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ፉአድ ገና ገለጹ።

በራሽያ ኡሊያኖስክ ግዛት እየተካሄደ በሚገኘው 10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ፉአድ ገና የተመራ ልዑክ ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል። ጉባኤው በብሪክስ ማዕቀፍ ስር የአባል አገራቱን የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ አላማ ያደረገ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። 10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ በትምህርትና ስልጠና፣ በሳይንስ፣በ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በጤና፣ በስፖርትና በኪነጥበብ ዙሪያ እየመከረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ጉባኤው በብሪክስ አባል አገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር የሚከፍት ነውም ብለዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሁሉም የብሪክስ አባል አገራት የተወከሉ የወጣት አመራሮችና ሚኒስትሮች እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ በጉባኤው ስትሳተፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ፉአድ ገና በነገው እለት በሚካሄደው የብሪክስ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይም እንደሚሳተፉ አያይዘው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ወጣቶች ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፎች ላይ እንደሚመከሩም አስተውቀዋል።

ከሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ይኸው አመታዊ ጉባኤ እስከ መጪው አርብ ድረስ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።

 

Please follow and like us: