የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገረ-መንግስት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይሠራል። ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት መንግስት ባለፉት አመታት አጥብቆ ሲሰራበት የቆየውና ዜጎችም ለዘመናት ሲጠየቁ የኖሩት በሀገራዊ ምክክር አማካኝነት መሰረታዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሳቤ አሁን ላይ ወሳኝ ሊባል በሚችል ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገረ-መንግስት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ መድረኮችን ሲያመቻችና የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ እንደሀገር በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች መሆናቸውን አንስተው አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋፆ ስለሚያበረክት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት ሚኒስትሯ አድንቀዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ከላፈው መጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያት በስምንት ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን የማሰባሰብ እና የማጠናቀር ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል። እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር የተሻለ ሀገር በመገንባትም ሆነ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አጀንዳዎቹ የአሁንና የወደፊት ሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት አሸናፊ ሆነን እንውጣ ከተባለ መመካከር አለብን በምክክሩም ሴቶችን ይዘን መውጣት አለብን። የሴቶች አጀንዳ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነውም ብለዋል።

የ’ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ፕሬዝዳንት ሳባ ገ/መድህን በበኩላቸው በአገራዊ የምክክር መድረክ በሴቶች ተገቢውን ውክልና አግኝተው የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱና በአገሪቱ የወደፊት እድል ላይ እንዲወስኑ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል ። የሴቶችን አጀንዳ ለብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮምሽነር ክቡር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ያስረከቡት የ’ጥምረት ለሴቶች ድምጽ’ ስራ አስፈፃሚዎች ናቸዉ።

Please follow and like us: