ጉባዔው በብሪክስ አባል አገራት ወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር ዕድል ፈጥሯል

10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባዔ በአባል አገራቱ መካከል ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር የከፈተ እንደነበር የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋዓድ ገና የተመራ ልዑክ ቡድን በቅርቡ በሩሲያ ኡልያኖስክ በተካሄደው 10ኛው የብሪክስ የወጣቶች ጉባዔ ተሳትፏል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋዓድ ገና፤ ኢትዮጵያ በጉባዔው የነበራትን ተሳትፎና አንደምታ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም፤ በጉባዔው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሁሉም የብሪክስ አባል አገራት የተወከሉ የወጣት አመራሮችና ሚኒስትሮች መሳተፋቸውን ገልጿል። ኢትዮጵያም የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏን ተከትሎ በጉባዔው ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏን ተናግሯል።

በትምህርትና ሥልጠና፣ ሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በጤና፣ በስፖርትና በኪነ-ጥበብ ዙሪያ ላይ ጉባዔው መምከሩን ጠቁሟል። ጉባዔው የአባል አገራቱን ወጣቶች በአንድ መድረክ በማሰባሰብ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲመክሩና በመፃዒ ዕድላቸው እንዲወያዩ በር ከፍቷል ነው ያለው። ወጣቶች በየአገራቸው ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ መደላደልን የፈጠረ መድረክ መሆኑንም ጠቅሷል።

ጉባዔው በአጠቃላይ በብሪክስ አባል አገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር የከፈተ እንደነበር የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወጣት ፉአድ ገና ገልጿል። ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ወጣቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከብራዚል፣ ከኢራን እና ከተባበሩት አረብ ኤመሬቶች የወጣት ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ከ40.1 ሚሊዮን በላይ የሀገራችን ወጣቶችን የሚወክል እና ወጣቶች በተደራጀ አግባብ መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ እንዱሁም በአገር ግንባታ ሂደት ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ተልእኮ አንግቦ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡

 

Please follow and like us: