የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጋር በጋራ በመሆን በጎፋ ዞን ለተጎዱ ወገኖች ከ4.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአልባሳትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጋር በጋራ በመሆን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ከ2.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአልባሳት ድጋፍና የ2 ሚሊየን የገንዘብ ድጋፍ አደርጓል ።

በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሀዘኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለት በስፍራው በመገኘት ጉዳቱ የደረሰባቸውን ወገኖች ከማጽናናት በተጨማሪ ከዘህ በፊት ቃል በገባው መሠረት ሀብት በማሰባሰብ 2.6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህል፣ የህፃናትና የአዋቂ አልባሳት፣ ብርድ ልብስ እንዲሁም የ2 ሚሊየን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። በቀጣይ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የውሀና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እኛን ለማፅናናትና ለመደገፍ መምጣቱ ያለውን ቤተሰባዊ ፍቅር ያሳያል ብለዋል። አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲያፅናና ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አውስተዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ለተጎጂ ወገኖች ላደረጉት ድጋፍም የክልሉ መንግስትና የጎፋ ዞን ምስጋና አቅርበዋል።

Please follow and like us: