የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዙሪያ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (Public-Private Dialogue) ተካሄደ ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዙሪያ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (Public-Private Dialogue) ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ከተውጣጡ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያዩ ።

 

በውይይት መድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዉይይቱ ላይ እንደገለፁት የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ አቅርቦትና ተደራሽነት የሚያረጋግጡ የስትራቴጂ ለውጦች እንዲደረጉ የሚያስችሉ ስራዎችን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ። በተለይ ደግሞ ምርቱ ከውጭ በሚገባበት ወቅት ከፍተኛ የቀረጥ ቅናሽ በማድረግና በፊት ከነበረበት ከ30 በመቶ ወደ 10 በመቶ በማውረድ ሴቶችና ታዳጊ ሴቶች በዝቅተኛ ዋጋ መጠቀም እንዲችሉ አበረታች እርምጃ መወሰዱንም ገልፀዋል ። በተጨማሪም ምርቱ በሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲመረትና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ በተናጠል የተጀመሩትን እንቅስቃሴዎች አቀናጅቶ መምራትና በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች በጋራ የሚፈቱበትን አዋጭ ስልትና ጠንካራ አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል።

ከዚህ አኳያ በተለይ በፈረንሳይ የልማት ድርጅት የተቀረፀውና ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካላት ሲከናወኑ የነበሩትን ተግባራት በተቀናጀ መንገድ የሚመራና ስራውን በበላይነት የሚያስተባብር ወሳኝ ባለድርሻ አካላትን የያዘ አብይ ኮሚቴ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን በመምራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

 

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የንፅህና መጠበቂያ እጦት እስከ ጤና እክል ድረስ የሚያደርስ መሆኑን ጠቅሰው ሚኒስቴር መስሪያቤታቸው ለማህበረሰቡ ከተለያዩ የጤና ማዕቀፎች ጋር በማቀናጀት ሰለ ንፅህና መጠበቂያና የወር አበባ ግንዛቤ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል። አብይ ኮሚቴው የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅን አስመልክቶ፡- እንደሀገር ያለውን አጠቃላይ አሰራር በመፈተሽ እንዲስተካከል ምክረ-ሃሳብ የማቅረብና በጥናት የተለዩ ችግሮች የሚፈቱበት የድርጊት መርሀግብር የማዘጋጀት ኃላፊነት ተሰጥቶታል ። ውይይቱ በአራት ዋና ዋና ዘርፎች – ማለትም በሕግ ቁጥጥር፣ በፋይናንስ፣ በስርጭት አውታሮች እንዲሁም በግንዛቤ እና በግንኙነት ሂደት ውስጥ ያሉትን መሰናክሎች በመለየት መፍትሄዎችን ለመንደፍ ያለመ ነው።

Please follow and like us: