“ወጣቶች ከስራ ጠበቂነት አስተሳሰብ በመውጣትና የቴክኖሎጂውን ዓለም በመቀላቀል ክህሎታቸውን ሊያዳብሩ ይገባል” – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ወጣቶች ከተረጂነትና ስራ ጠበቂነት በመውጣትና የቴክኖሎጂውን ዓለም በመቀላቀል ክህሎታቸውን አዳብረው ለሀገር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

የዓለም ወጣቶች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ “ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዘላቂ ልማት ግቦች” በሚል እየተከበረ ይገኛል። በወቅቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ የወጣቶች ቀን የሚከበረው ወጣቶች ለሀገራቸው፣ ለአህጉራቸውና ለአለም ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና ያበረከቷቸውን አስተዋጽኦዎች ከመዘከር ባለፈ ሀገራት ወጣት ተኮር ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ያከናወኗቸውን ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ህብረሰተቡ እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው። የዓለም ዓቀፍ የወጣቶች ቀን መከበሩ ለአዲሱ ትውልድ የተሻለ ዓለም ለመገንባት፣ ከድህነት ለመውጣት፣ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ወጣቱ ያለውን እይታና ግንዛቤ ለማዳበር እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

የተሻለና ቀጣይነት ያላው ልማት በሀገሪቱ ለማምጣት የፈጠራ አስተሳሰብን እና ተግባርን ማበረታታት እንዲሁም የዓለም ቀጣይ እጣ ፋንታ ብሩህና በተስፋዎች የተሞላ እንዲሆን ከማስቻል አንጻር ጉልህ ድርሻ አለው ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ከታሰበለት ጊዜ አስቀድሞ እውን ለማድረግ ወጣቱ ወርቃማ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም በቴክኖሎጂ በመታገዝ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች ዙርያ ያለውን ተሳትፎ ማጠናከርና ማስቀጠል እንዳለበት አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል። ወጣቶች ከተረጂነትና ስራ ጠበቂነት አስተሳሰብ በመውጣትና የቴክኖሎጂውን ዓለም በመቀላቀል ክህሎታቸውን አዳብረው ለሀገር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አሳስበዋል። በወጣቶች አማካኝነት የተሰሩ የዲጂታል ፈጠራ ውጤቶችን የያዘ ኤግዚቪሽን ቀርቧል።

Please follow and like us: