የሴቶችና ማህበራዊ ሴከተር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና አደረጃጀቶች በቢሾፍቱ ከተማ ዳሎታ ተራራ ላይ ችግኝ ተከላ በማካሄድ አሻራቸውን አኖሩ

(አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17/ 2016 ዓ.ም) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች እና የክልል የሴክተር ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ አደረጃጀት ተወካዮቸ በቢሾፍቱ ከተማ ዳሎታ ተራራ ላይ ችግኝ ተከላ በማካሄድ አሻራቸውን አኑረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተሰፋዬ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል። የምንተክለው ችግኝ የተጎዳን አካባቢ ለማከም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ የሚሆን የተሻለ መልከዓ ምድር ትተን ለማፋለፍ ያግዛል ብለዋል። ችግኞችን መትከል የመጨረሻ ግብ አይደለም ያሉት ክብርት ሚኒስትር የተተከሉትን ችግኞች በአግባቡ መንከባከብ፣ ማጽደቅና ለፍሬ ማብቃት ይገባል ብለዋል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣና በጋራ እንዲረባረብም መልዕክት አስተላልፈዋል። የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል በሆነው በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ በመገኘት አሻራቸውን በማኖራቸውና ለቀረበው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠታቸውን መደሰታቸውን ገልፀዋል።
Please follow and like us: