ለተፋጠነ ሀገራዊ እድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በቅንጅት መስራትና በቁርጠኝነት ማገልገል ይጠበቅብናል – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ለተፋጠነ ሀገራዊ እድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በቅንጅት መስራትና በቁርጠኝነት ማገልገል ይጠበቅብናል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሴክተር ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህዝቡን ማዕከል በማድረግና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በተካሄደ ሰፊ ርብርብ በየዘርፉ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር በመመለስ፣ ወላጆቻቸውን ያጡና አቅም ደካማ ወገኖችን በመደገፍና በሌሎችም መስኮች አበረታች ስራዎች መሰራቱን አስታውቀዋል።

ሆኖም ሴክተሩ ሰፊ፥ የስራ ባህሪውም ዘርፍ ዘለል በመሆኑ በየዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና የዜጎችንም ጥያቄ በሚያጠግብ መልኩ ለመመለስ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ዜጎች በየዘርፋ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማሳደግ አኳያ የተቋማት አካቶ ትግበራ ስልቱ ስኬታማ እንዲሆን ተገቢውን የክትትልና ድጋፍ መስራትና ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባልም ብለዋል። በመዋቅር፣ በአደረጀጀት፣ በአመለካከት፣ በመረጃ አያያዝ ረገድ የሚስተዋሉትን ችግሮች በዘላቂነት መፍታትና የተዘሩጉ የአሰራር ማዕቀፎችንም በአግባቡ በስራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ አፅዕኖት ሰጥተዋል።

በሴክተሩ የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልፀው በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት ሴክተሩ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል። እንደሀገር ለተፋጠነ እድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በቅንጅት መስራትና በቁርጠኝነት ማገልገል ይጠበቅብናል ብለዋል።

 

Please follow and like us: