የሴቶችን ተጨባጭ የኢኮኖሚ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩኤን ውመን እና አክሽን ኤድ ጋር በመተባበር 3ኛው ሀገር አቀፍ የሴቶች ኢኮኖሚ ማብቃት ፎረም አካሂዷል።

በመድረኩ ከፌደራልና ከክልል መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በመወከል ንግግር ያደረጉት የሴቶች መብት ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ታደሰ በዚሁ ጊዜ፤ ሴቶች ያላቸውን እምቅ አቅም በሚገባ አውጥተው እንዲጠቀሙና በመረጡት መስክ መስራት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ከመለወጥ ባለፈ ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ እና ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ ብለዋል።

ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን መብት ለማስከበር፣ በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ሆኖም የሴቶችን ተጨባጭ የኢኮኖሚ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ አለም አቀፍና አገር በቀል የልማት አጋራት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የግል ባለሀብቶች እና ሌሎችም በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮች የጋራ ትብብርና ርብርብን የሚጠይቅ ተግባር መሆኑ አንስተዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንዲሰሩ አቶ ስለሺ ታደሰ መልዕክት አሰተላልፈዋል።

በዩኤን ውሜን የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ስመኝ ኩማ በበኩላቸው እንደሃገር የተቋቋመውን የሴቶች የኢኮኖሚ ማጎልበት ፎረም በማጠናከር ወደፊት ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ያለብንን የቅንጅትና ትብብር ክፍተቶች በመቅረፍ እንዲሁም የስራ ድግግሞሽና የሀብት ብክነት ለማስቀረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን መወጣት እንደሚ አሳስበዋል፡፡

የአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ትነበብ ብርሃኔ በበኩላቸው እንደአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ከስርዓተ-ጾታ እኩልነት ባለፈ በርካታ የልማት ስራዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ የልማት ስራዎችም ለሴቶች ብድር አገልግሎት በመስጠት፣ የስርዓተ-ጾታ እኩልን እንዲሰፍን በማድረግ፣ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ፍትህ በማረጋገጥ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎችን በመስራት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በሴቶች የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ ላይ የሚያተኩሩ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከቢሾፍቱ አካባቢ በትናንሽ ንግዶች ላይ የተሰማሩ ሴቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

 

Please follow and like us: