በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በተሟላ መንገድ ጤናቸው እንዲጠበቅ በተገቢው መንገድ መከታተልና መደገፍ ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በተሟላ መንገድ ጤናቸው እንዲጠበቅ በተገቢው መንገድ መከታተልና መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አምስተኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ጉባኤ “ተደራሽነትና ጥራት፣ ምላሽ ሰጪ የጤና ሥርዓት ለሁሉም የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች” በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመርኃ ግብሩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች ታድመዋል። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ወጣትነት ወርቃማ የእድሜ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል። የሕይወታቸው ሂደትና ዑደት ልዩ ትኩረት የሚፈልግበት መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ወቅት በአግባቡ ካልተያዘ ለተለያዩ የጤናና ማኅበራዊ ችግሮች የሚጋለጡበት መሆኑን ተናግረዋል። በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በተሟላ መንገድ ጤናቸው እንዲጠበቅ በተገቢው መንገድ መከታተልና መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚንስቴሩ ወሳኝ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸው ለወጣቶች አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል። የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በጤና ላይ የሚሰሩና የሚወጡ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህንንም ተከትሎ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች በጤና ላይ ያላቸውን እውቀትና ተሳታፊነት የሚያሳድጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። አፍላ ወጣትነት ለብዙ ማኅበራዊና የጤና ችግሮች ተጋላጭ የእድሜ ክልል በመሆኑ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

 

Please follow and like us: