ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሰራሩንና አገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሪፎርም ቀንን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት!” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አካሂዷል።

ጳጉሜ 2 – የሪፎርም ቀንን ምክንያት በማድረግ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን በመከላከልና ምላሽ ሠጪ ተግባራት ዙሪያ ግንዛቤ በሚያስጨበጥና ውይይት በማካሄድ እንዲሁም ቀሪ ጊዜን በስራ ላይ በማሳለፍ ዕለቱን አስበው ውለዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደሀገር የተካሄዱና አሁንም በሂደት ላይ የሚገኙ ጉልህ የሪፎርም ስራዎች መኖራቸውን፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አሰራሩንና አገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች በማከናወን ላይ የሚገኝ መሆኑ በስራ ኃላፊዎች ተገልጿል።

እንደሴክተር በየዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች እንዲሳኩና ዜጎችም የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች በላቀ ተነሣሽነት እንዲሠሩና የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክት ተላልፏል። በሌላ በኩል በአገራችን በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ፣ መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ እንዲሁም መሰል ክስተቶች ሲያጋጥሙ ማህበረሰቡ ተቋቁሞ ማለፍ የሚችልበትን አቅም ለማጎልበት ታስቦ በአለም ባንከ የበጀት ድጋፍ (Response – Recovery – Resilience for Conflict Affected Communities in Ethiopia (3R-4-CACE) Project) የሚል ፕሮጀክት ተቀርፆ በ5 ክልሎችና በ40 ወረዳዎች እየተገበረ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ዲያና ወንድሙ በዚሁ ጊዜ አስገንዝበዋል፡፡

እንደሀገር በተለይ በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያት ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችና ህፃናትን መደገፍ ላይ ትኩረት ያደረገው የፕሮጀክቱ ክፍል በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት እንደሚመራ እና በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱን በሙሉ አቅም ተግባራዊና ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በመሆኑም መላው ሰራተኛን ጨምሮ የሴክተሩ አስፈፃሚ አካላት ለስኬታማነቱ በጋራ እንዲረባረቡ በተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጥሪ ቀርቧል።

 

Please follow and like us: