የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከቻይና ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር በማህበራዊ ጥበቃና ማህበራዊ ዕሴቱ እየጎላ በመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሄዱ

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከቻይና ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር በማህበራዊ ጥበቃና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በቻይና የህብረተሰብ አገልግሎት ዲፓርትመንት የማዕከላዊ ኮሚቴ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ዛሆ ሺቶንግ (ዶ/ር) የተመራውን ልዑካን ቡድን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የስራ ኃላፊዎቹ በሁለቱ ሀገራት በማህበራዊ ጥበቃና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ ባሉ ጥረቶችና ስኬቶች፣ ዘርፋን በተደራጀ አመራር ለመምራት በተወሰዱ እርምጃዎችና በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የቻይና ባለሃብቶች ተሳትፎና በቀጣይ በጋራ መስራት በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ዙሪያ ሰፊ ውይይትና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

በውይይታቸውም፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት፥ ቻይናና ኢትዮጵያ በመከባበርና በትብብር ላይ የተመሠረተ ለአመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አብራርተዋል። የቻይና ካምፓናኒዎች እና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና፣ በማኑፋክቸሪግ እና በሌሎችም መስኮች እያደረጉት ያለው የስራ እንቅስቃሴ የዚሁ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሴክተሩ ተደራሽ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ደግሞ ደሃ እና ለችግር ተጋላጭ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። አሁን ላይ በስፋት እየተተገበረ የሚገኘውና ማህበራዊ እሴቱ እየጎላ የመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጋራ ሃብታችንን በጋራ ለመጠቀምና ጠቃሚ እሴቶቻችንን ለማጎልበት መሰረት መሆኑንም ገልፀዋል። በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር ብቻ 24 ሚሊዮን ወጣቶች በ14 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ሀገራቸውንና ማህበረሰባቸውን የሚጠቅም ተግባር ማከናወን መቻላቸው ትልቅ ስኬት እንደነበረም አንስተዋል፡፡

የበጎ-ፈቃድ አገልግሎቱ ወጥና ተደራሽ እንዲሆን እንዲሁም በተደራጀ አግባብ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር ብሔራዊ የበጎ-ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ መዘጋጀቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ውይይቱም በቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ብሎም በማህበራዊ ጥበቃ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በትምህርትና በአቅም ግንባታ ስልጠና ዘርፎች ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑንም ጠቁመዋል። በተጠቀሱት ዘርፎች በትብብር ለመተግበር የተጀመረው ውይይት ወደ ተግባር እንዲሸጋገርም ሚኒስቴሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የቻይና የህብረተሰብ አገልግሎት ዲፓርትመንት የማዕከላዊ ኮሚቴ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ዛሆ ሺቶንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የበጎ – ፈቃድ አገልግሎት በቻይና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የማህበራዊ ጥበቃና የበጎ-ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

Please follow and like us: