ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማኅበራዊ ጥበቃን በገንዘብ ለመደገፍ ጥሩ ዕድል መፍጠሩ ተገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ማኅበራዊ ጥበቃን በገንዘብ ለመደገፍ ጥሩ ዕድል መፍጠሩን የአለም ባንክ ተወካዮች ገለጹ፡፡

ይህ የተገለፀው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ ተወካዮች ጋር በማህበራዊ ጥበቃ የፖሊሲ ማሻሻዎች፤ቀጣይ ስለሚደረገው የማሕበራዊ ጥበቃ ኮንፍረንስና የከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችን በቅንጅት መደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት አለም ባንክ ለፖሊሲ ማሻሻያው እንዲሁም አጠቃላይ የማህበራዊ ጥበቃ ስራዎች ላይ እያደረገ ያለውን ድጋፍን አድንቀው ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመድረስና በቅንጅት ከመስራት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

ሚንስትሯ አክለውም ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደስራዉ ባለቤት እስካሁን ከሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በጋራ በመሆን ከማህበራዊ ጥበቃ ምዝገባ ሂደት እስከ ፖሊሲ ማሻሻል ድረስ የተለያዩ ስራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው ለዚህም የአለም ባንክን ትብብር ከመቼውም ጊዜ በላይ እስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአለም ባንክ ተወካዮች በበኩላቸው አሁን ላይ ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማኅበራዊ ጥበቃን ጨምሮ ሌሎች የልማትና የትብብር መስኮች ላይ በቅንጅት ለመስራት እንደሚያስችል ገልፀው ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ዘርፍ ለሚሰራው ስራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

 

Please follow and like us: