ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን መደገፍና ማጠናከር ይገባል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የሸገር ከተማ ከንቲባ ክቡር ዶክተር ተሾመ አዱኛ ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት ማህበር ያስገነባውን ‘የግራር መንደር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት ማዕከል’ በዛሬው ዕለት በይፋ መረቀው ከፍተዋል።

በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ የህጻናት ጤናማና ደስተኛ እድገት የሚፈታተኑ አያሌ ችግሮች በመኖራቸው የተነሳ ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ጣፋጭ የህይወት ሂደት በትክክል እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል፡፡ የነገይቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ የሆኑት ህፃናት በእውቀት፣ በመልካም ጤናና ሰብዕና ታንጸው እንዲያድጉ አስፈላጊው ቤተሰባዊ፣ ማህበራዊና ተቋማዊ ድጋፍና ክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ መንግስት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት ጉዳይ በተለያዩ ፖሊሲዎች ውስጥ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የህፃናት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመለወጥ የሚያግዙ ንቅናቄዎችን እያካሄደ ይገኛል ብለዋል። ይህ ማዕከል መገንባቱና ለአገልግሎት መብቃቱም በተለይ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህጻናት እና ለቤተሰቦቻቸው ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል። ተስፋ አለመቁረጥ፣ ፀንቶ መስራትና በቅንጅት መረባረብ ከዝቅታ ወደ ከፍታ እንደሚያደርስ ያለሙትን እውን ማድረግ እንደሚያስችል ከፕሮጀክቱ መስራች፣ አመራሮችና ሠራተኞች መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።በሀገራችን ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናት ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር ውሱን በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን ማጠናከርና መደገፍ ይገባል ሲሉም ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልፀዋል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው፤ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማህበሩ እያደረገ ላለው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ትኩረት ለሴቶችና ህፃናት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር አሳየች ይርጋ፤ ላለፋት 17 ዓመታት ከ12 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን የደገፉ አካላትን በሙሉ በተጠቃሚ ወገኖች ስም አመስግነዋል።

 

Please follow and like us: