በግጭት ምክንያት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍና ለማቋቋም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል – ክብርት ሂክማ ከይረዲን

በግጭት ምክንያት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍና ለማቋቋም የሚያግዝ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን እንደተናገሩት፤ በግጭት ወቅት ፆታዊ ጥቃት በሰፊው እንደሚፈፀምና ሴቶችና ህፃናትም ይበልጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። ፆታዊ ጥቃት ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተቀናጀ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  ለዚህም የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በተለይ በግጭት ምክንያት ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ማህበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማጠናከር እና ተጎጂ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል (3R-4-CCE Response, Recovery, Resilience for Conflict Affected Communities in Ethiopia) የሚል የአምስት አመት ፕሮግራም በማዘጋጀት በአምስት ክልሎች እና በ40 ወረዳዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀፓይጎ ከተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል እና አፋር ክልል እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት የሚገኝበትን ደረጃ ለመገንዘብ የሚረዳ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም በግጭት ምክንያት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍና ለማቋቋም የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ዜጎች የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ አፅዕኖት ሰጥተዋል።

ጾታዊ ጥቃት በሴቶችና ህጻናት ላይ አካላዊ ጉዳት የሚያደርሱ፣ የከፋ የጤና እክል የሚያስከትሉ፣ ውስብስብና ድርብር ለሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚዳርጉ ብቻም ሳይሆን ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላም በተጎጂዎች አእምሮና ስነልቦና ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠበሳ በቀላሉ የሚሽር ባለመሆኑ አመለካከቱንም ሆኑ ድርጊቱን አስቀድሞ ለመከላከልና ለማስቆም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡  በመድረኩ የዳሰሳ ጥናት ውጤቱ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚሰጠውን የህክምና፣ የአእምሮ፣ የስነልቦና፣ የማህበራዊ፣ የምክር፣ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዱ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች በአውደ ጥናቱ መመላከቱ ተጠቁሟል።

 

Please follow and like us: