የህፃናት ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በኮሎምቢያ ቦጎታ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በተዘጋጀው ሀገራዊ ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ

በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ መጪው ህዳር ወር ላይ በሚንስትሮች ደረጃ በኮሎምቢያ ቦጎታ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በተሰናዳው ሀገራዊ ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ።

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት፤ የህፃናት ጥቃትን ከማውገዝ በዘለለ ጥቃት እንዳይደርስ መሰራት እንዳለበት ገልፀዋል። ክብርት ሚኒስትሯ ጥቃትን ከማውገዝና አስቀድሞ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የህግ ክፍተቶችን በመለየት እንዲሻሻሉ፣ በጥቃት አድራሾች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድና ተጎጂዎችም ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የህጻናት መብቶች ድንጋጌዎችን ተቀብላ በማጽደቅና የሕግ አካል በማድረግ የሕጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን፣ ፕሮጀክቶችንና የማስተግበሪያ ስልቶችን በመንደፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝም ጠቁመዋል። እንደሀገር ያሉ የህግ ክፍተቶችን በመፈተሽ እንዲሻሻሉ ብሎም ወጥ የሆነ ምላሽ ሰጪ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋትና ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። ኮንፈረንሱ የተገኙ ሀገራዊ ስኬቶችን ለማሳየትና የሀገርንም ገፅታ ለመገንባት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ከሌሎች ሀገራት ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ የምንወስድበት እንዲሁም በቀጣዮቹ አምስት አመታት ውስጥ ችግሩን ለማስቆም የሚቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ቃል ኪዳን የምንገባበት በመሆኑ መድረኩ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ በበኩላቸው ዩኒሴፍ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እ.ኢ.አ በ2030 የህፃናትን ጥቃት ለማስቀረት የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።

 

Please follow and like us: