ታዳጊ ሴቶች እያጋጠማቸው ያለውን ፈተና ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተን መሰራትና በጋራ መረባረብ ይገባል

የዘንድሮው አለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን በሀገራችን ለ13ኛ ጊዜ “ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው” በሚል መሪ መሪ ቃል በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ታዳጊ ሴቶች እያጋጠማቸው ያለውን ፈተና ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተን መሰራትና በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል። የአገራችን የወደፊት ተስፋ እንደመሆናቸው ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዲችሉ ከቤተሰብ ጀምሮ መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። ዛሬ ያልዘራነውን ነገ ማጨድ አንችልም ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ የተሻለች ሀገር ለመገንባት ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራትና ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል። ወደፊትም በሴቶች መብት ዙሪያ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አበክሮ ይሰራል ብለዋል። ታዳጊና ወጣት ሴቶችም አቅማቸውን እንዲያጎለበቱ፣ ጠንካራ ስነልቦና እንዲያዳብሩና አላማቸውን ለማሳካት እንዲተጉ መክረዋል። ህልማቸውን ከሚያደናቅፉ እና ከትምህርት ገበታቸው ወደ ኃላ ከሚያስቀሩ የአቻ ግፊቶችም እንዲጠበቁ አደራ ብለዋል።

የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከብርት ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው ሴቶች ሊደርሡበት ከሚገባው ደረጃ እንዳይደርሱ ከገደቡዋቸው ምክንያቶች መካከል የስርዓተ ፆታ እኩልነት አለመስፈን፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መንስዔ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች አምራች የልማት ኃይል የሆኑትን ታዳጊ ሴቶች እንዲሁም የነገ የሀገር አለኝታ የሆኑት ታዳጊ ህጻናትን መፃዒ ተስፋ ከማጨለም ባሻገር በሁለንተናዊ መልኩ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በመግታት ትውልድን በየደረጃው እንደሚፈትኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓብይ ምክንያትም ታዳጊ ሴቶች በማንኛውም መልኩ ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎችና አስተዋኣቸው ተገቢው እውቅና እንዲሰጣቸው ለማድረግ ታስቦ የአለም የታዳጊ ሴት ልጆች ቀን በየአመቱ እንዲከበር መወሰኑን አስገንዝበዋል፡፡

ቀኑ ታዳጊ ሴቶች ድምፃቸውን ጎልቶ የሚሰማበት፣ ተሳትፏቸውን የሚጠናከርበት፣ ስጋትና ጥያቄያቸውን አንስተው የሚወያዩበት እንዲሁም ጠቃሚ ልምዶችን እርስ በእርስ መለዋወጥ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ያለቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ታዳጊ ሴቶችና ወጣት ሴቶችን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት ተገኝተዋል።

 

Please follow and like us: