የገጠር ሴቶችን በትምህርትና በቴክኖሎጂ መደገፍና ማብቃት ወሳኝ ነው

የገጠር ሴቶችን በትምህርትና በቴክኖሎጂ መደገፍና ማብቃት ወሳኝ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

ዓለም አቀፉ የገጠር ሴቶች ቀን “በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን በትምህርትና በቴክኖሎጂ ተደራሽነት ማብቃት!” በሚል መሪ ሃሳብ በአፍሪካ ህብረት እየተከበረ ይገኛል። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የገጠር ሴቶችን በትምህርትና በቴክኖሎጂ መደገፍና ማብቃት ወሳኝ ነው። የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት፣ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ችግሮች የገጠር ሴቶችን ከሚፈትኑት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።የገጠር ሴቶች የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠማቸው ቢሆንም የቤተሰብ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

ሴቶች በተሰማሩበት ሙያ ውጤታማ እንዲሆኑ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በማስፋት የገጠር ሴቶችን ሕይወት የማሻሻል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የገጠር ሴቶችን የመሬት ባለቤትና የፋይናንስ ተደራሽ መሆን የሚያስችሉ የሕግና አሠራር ሥርዓቶች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም እንዲሁ። በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ሴቶችን በመደገፍ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ አካባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ በበኩላቸው፤ ለአፍሪካ ግብርና የጀርባ አጥንት የሆኑ የገጠር ሴቶችን ማብቃት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተዋል።የአፍሪካ የገጠር ሴቶችን ሕይወት ለማሻሻል ጥራት ያለው ትምህርትን ማዳረስና ቴክኖሎጂን ማስፋት ለነገ የማይባል መሆኑንም ነው ያነሱት። የገጠር ሴቶች በግብርናው መስክ ከቤተሰብ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምርት እንዲያመርቱ መደገፍ ይገባል ብለዋል። ለአህጉሪቱ ዘላቂ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ የገጠር ሴቶች ያላቸውን ሚና እንዲወጡ የህብረቱ አባል አገራት በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

 

Please follow and like us: